18/02/2026
የአውሮጳ እግር ኳስ ማሕበር በእንግሊዘኛ ምህጻሩ (UEFA) በብራዚላዊ የሪያል ማድሪድ ኮከብ ቪኒሺየስ ጁንየር ላይ ደረሰ የተባለውን የዘረኝነት ጥቃት ሊመረምር ነው።
ማሕበሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፥ የሪያል ማድሪዱ አጥቂ ቪኒሺየስ ጁኒየር የቤንፊካው ጂያንሉካ ፕሪስቲያኒ ትናንት ማክሰኞ ምሽት ሊዝበን በተካሄደው የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ላይ «የዘረኝነት ስድብ ሰድቦኛል» በማለት ላቀረበው ክስ «አድሎአዊ ባህሪን» በተመለከተ ምርመራ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ምሽቱን በተደረገው የጥሎ ማለፍ ማጣሪያ የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያ ቪኒሺየስ ከቤነፊካዊ ተጫዋች ፕሪስቲያኒ ጋር ግጭት ውስጥ ከገባ በኋላ ለፈረንሳዊው ዳኛ ፍራንሷ ሌቴክሲየር አቤቱታ ማቅረቡን ተከትሎ ጨዋታው ከ10 ደቂቃ በላይ ተቋርጦ ነበር።
በተቻዋቾቹ መሃል ግጭቱ የተፈጠረው ቪኒሺየስ ሪያል ማድሪድን 1 ለ 0 አሸናፊ ያደረገችውን ብቸኛ ግብ ካስቆጠረ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ነው።
ቪኒሺየስ ግቡን ካስቆጠረ በኋላ በቤንፊካ ደጋፊዎች ፊት «ወጣ ባለ ጭፈራ» ደስታዉን በመግለጹ የቢጫ ካርድ ተመልክቷል።
ቪኒሺየስ ከፕሪስቲያኒ የስድብ ድምጽ ከሰማ በኋላ ወደ ዳኛው በመሮጥ በስፓኒሽ ቋንቋ «ሞኖ» (ዝንጀሮ) የሚል ስድብ እንደሰደበው አመልክቷል።
የ20 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ኢንተርናሽናል የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ፕሪስቲያኒ ለቪኒሺየስ የሆነ ነገር ሲናገር አፉን በልብሱ ሸፍኖ የነበረ ሲሆን የዘረኝነት ስድብ መሳደቡን ግን አስተባብሏል።
የሪያል ማድሪዱ እንግሊዛዊ ተከላካይ ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ ድርጊቱ ምሽቱን እንዳበላሸባቸው ገልጿል።
ድርጊቱን «አስጸያፊ» ሲል የገለጸው ተጫዋቹ «የሆነው ነገር ለእግር ኳስ ትልቅ ውርደት ነው» ብሏል።
የማድሪዱ አጥቂ ኪሊያን ምባፔ በበኩሉ ፕሪስቲያኒ ከጨዋታ እንዲታገድ ጥሪ አቅርቧል።
«በአውሮጳ ምርጥ ውድድር ላይ እየተጫወተ እንዲህ ያለ ባህሪ የሚያሳይ ተጫዋችን አንቀበልም» ብሏል።
ምባፔ አክሎም «ይህ ሰው ዳግመኛ በሻምፒዮንስ ሊግ የመጫወት መብት ሊኖረው አይገባም» ሲል ብርቱ ተቃዉሞውን አሰምቷል።
የቤንፊካው አሰልጣኝ ሆሴ ሞሪንሆ ግን ቪኒሺየስ ግቧን ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን የገለጸበት መንገድ ደጋፊዎችን እና ተጫዋቾችን ለቁጣ አነሳስቷል በሚል ተችተውታል።
«ኪክ ኢት አውት» የተባለው የእንግሊዝ የእግር ኳስ ጸረ-መድሎ ተቋም የሞሪንሆን ምላሽ በመተቸት አሰልጣኙን «እውነታውን በማድበስበስ» ከስሷቸዋል።
ተቋሙ በመግለጫው «ማንኛውም ሰው በእግር ኳስም ሆነ በየትኛውም ቦታ መድልዎ ሲደርስበት ካመለከተ የመጀመሪያው ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ተጎጂውን ማዳመጥና ድጋፍ መስጠት ነው» ብሏል።
የክስተቱን ትኩረት «ቪኒሺየስ ደስታውን ወደ ገለጸበት ወይም ወደ ክለቡ በማዞር የቀረበውን አቤቱታ ችላ ማለት እውነታውን የማድበስበስ ተግባር ነው» ሲል እየተባባሰ የመጣውን የዘረኝነት ጥቃት አውግዟል።