18/09/2026
የኦሞ ስኳር ፋብሪካዎች አመራሮች በወንጂ/ሸዋ ስኳር ፋብሪካ የሥራ ልምድ ልውውጥ ጉብኝት አደረጉ።
የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕን ጨምሮ የኦሞ ስኳር ፋብሪካዎች ቁጥር 1/3 እና 2 ከፍተኛ አመራሮች፣ ዋና ሥራ አስኪያጆችና የዘርፍ ኃላፊዎች በታሪካዊው ወንጂ/ሸዋ ስኳር ፋብሪካ የሥራ ልምድ ልውውጥ ጉብኝት አደረጉ። የልዑካን ቡድኑ በፋብሪካው ተ/ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አወል ሁሴንና በማኔጅመንቱ አባላት ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎለት፣ ፋብሪካው ከተደቀነበት ከባድ የመውደቅ አደጋ ተላቆ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ማገገምና ውጤታማነት የተመለሰበትን ሂደት በአካል ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚና የልዑካን ቡድኑ መሪ አቶ ዲንሳ አብደና በወንጂ/ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ተ/ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አወል ሁሴን የተመራው የሥራ ልምድ ልውውጥ ጉብኝት፣ በዋናነት በፋብሪካ ሥራዎች፣ በሸንኮራ አገዳ እርሻ አስተዳደር፣ በጋራዥና በጥገና ሥራዎች፣ እንዲሁም በተጎዳኝ ልማት ዘርፎች የተገኙ ልምዶችን ለመለዋወጥ ያለመ ነበር።
በጉብኝቱ ወቅት የፋብሪካው አመራሮች ከሸንኮራ አገዳ ልማት ባሻገር በፋብሪካው የውስጥ አቅም እየተከናወኑ ያሉ የተጎዳኝ ልማት ሥራዎችን አስጎብኝተዋል። በዚህም በፋብሪካው አቅም 40 የዓሣ ኩሬዎች ተገንብተው የዓሣ እርባታ እተከናወነና ምርቱም ወደ ገበያ መቅረብ መጀመሩን ተመልክተዋል። በተጨማሪም የማር፣ የእንቁላል፣ የወተት፣ የማደለብ፣ የእንስሳት መኖ ማቀነባበር፣ የፓፓዬና የሙዝ ልማት ሥራዎች ተጎብኝተዋል። እነዚህን የልማት ዘርፎች ለማጠናከርም የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽን በፋብሪካው አቅም መተከሉ ተገልጿል።
ሌላው የጉብኝቱ ትኩረት የፋብሪካው የእርሻ አስተዳደርና የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ሲሆን ፋብሪካው ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ወጪን ለመቀነስና የሥራ አፈጻጸምን በተጨባጭ መረጃ ለመምራት የዘረጋቸው የማሳ አስተዳደር፣ የመረጃ አያያዝና የክትትል ሥርዓቶች ቀርበዋል። በተለይም የማሳ ሁኔታን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መከታተል፣ የሥራ ክፍተቶችን በመረጃ መለየትና በወቅቱ የማስተካከያ ውሳኔ መስጠት እንደ ዋና የአሠራር ልምድ ተገልጿል።
በተጨማሪም በመጪው የምርት ዘመን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በፋብሪካና በመስክ መሣሪያዎች ላይ እየተከናወኑ ያሉ የክረምት ዝግጅት፣ የጥገናና የማሻሻያ ሥራዎች ተመልክተዋል። በጋራዥ የማሽነሪዎችና የተሽከርካሪዎች ጥገና፣ የመለዋወጫ እቃዎች አጠቃቀምና የጥገና ሥራዎች አመራር ላይ የተገኙ ልምዶችም ተጋርተዋል።
የጉብኝቱን መጠናቀቅ ተከትሎ በም/ዋ/ስ/አስፈጻሚ በአቶ ዲንሳ አብደና እና በአቶ አወል ሁሴን የተመራ የማጠቃለያ ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱም የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና መስሪያ ቤት ከፍተኛ አመራሮች እና የኦሞ ስኳር ፋብሪካዎች አመራሮች እንዲሁም የወንጂ/ሸዋ ስኳር ፋብሪካ አመራሮች በጉብኝቱ በተገኙ አንኳር ተሞክሮዎች ላይ ሰፊ የጋራ ውይይት በማድረግ ለወደፊቱም በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሳል። በመጨረሻም ልዑካን ቡድኑ ወንጂ/ሸዋ ስኳር ፋብሪካ የኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪ ፈር ቀዳጅና አርአያ መሆኑን ገልጸው፣ ፋብሪካው ከከባድ ችግሮች ተላቆ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሳየው መነቃቃትና የአፈጻጸም ማሻሻያ ለቀጣይ ሥራቸው ጠቃሚ ትምህርት መሆኑን አስረድተዋል።