12/11/2025
ስምንት ሀገራት ኢትዮጵያ ገብተዋል
=======
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የሴካፋ ዞን የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የማጣርያ ውድድር ተሳታፊ የሆኑ ሀገራት አዲስ አበባ ገብተዋል።
አስር ሀገራት የሚሳተፉበት መድረክ ከኅዳር 6 ጀምሮ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ የሚደረግ ሲሆን እስከ ዛሬ ድረስ ስምንት ሀገራት ኢትዮጵያ እንደደረሱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አሰውቋል።
የሱዳን ብሔራዊ ቡድን ልዑክም በነገው ዕለት ኢትዮጵያ እንደሚገባ ይጠበቃል።
ቡድኖቹ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ የእድሜ ተገቢነት (MRI) ምርመራ በማከናወን ላይ የሚገኙ ሲሆን ምርመራ ካጠናቀቁ በኋላ ዩጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ታንዛንያ፣ ሱዳን እና ጅቡቲ የምድብ ጨዋታቸውን ወደሚያደርጉበት ድሬዳዋ ያመራሉ ተብሏል።
በሁለት ምድብ ተከፍሎ በሚደረገው ጨዋታ አስተናጋጇ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማልያ እና ሩዋንዳ ደግሞ የምድብ ጨዋታቸውን በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስቴዲየም የሚያከናውኑ ይሆናል።