28/07/2025
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽንና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ሁናቸው ታዬ ሚሊኒየም አዳራሽን አሰመልክቶ ለሚዲያዎች የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፦
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር የሚገኘው አዲስ ፓርክ እና ማኔጅመንት በተለምዶ ሚሊኒየም አዳራሽ እየተባለ የሚጠራው በኢትዮዽያ ውስጥ ከሚገኙ ግዙፍ አዳራሾች መካከል ግንባር ቀደሙ መሆኑ ይታወቃል።
ሚሊኒየም አዳራሽ የኢትዮዽያ ሚሊኒየምን ታሳቢ አድርጎ በዘመናዊ መልኩ ተገንብቶ የተለያዩ አገልግሎቶችን ሲሰጥ የቆየ ግዙፍ አዳራሽ ነው።
ይህ የሚሊኒየም አዳራሽ ኢትዮዽያ ውስጥ የነበሩ ጥሩም ሆኑ መጥፎ ጊዜያቶች ሁሉንም በአንድ በማሰባሰብ ትልቅ ሚና የተጫወተ ነው። አሁንም በመጫወት ላይ ይገኛል።
እስከ 25 ሺህ ሰዎችን በአንድ ጊዜ የማስተናገድ አቅም ያለው የሚሊኒየም አዳራሽ 20 ሺህ ስኩየር ሜትር ስፋት ላይ ያረፈ ነው።
በዘመናዊ ሳውንድ ሲስተም፣ ዲጅታል ስክሪን፣ የመድረክ መብራቶች እና ዘመናዊ ፈርኒቸርና የኤግዚቢሽን ቁሳቁሶች የተደራጀው ይህ አዳራሽ እስካሁን ድረስ በርካታ ዝግጅቶችን አስተናግዷል።
እንደ ሀገር በኢትዮዽያ ተከስቶ በነበረው የኮቪድ 19 ችግር ወቅት ሙሉ በሙሉ ለህክምና አገልግሎት መስጫነት መዋሉም ይታወሳል።
ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮግራሞች፣ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች፣ ኤግዚቢሽኖች፣ ሀይማኖታዊ ፕሮግራሞች፣ ምርቃቶች እንዲሁም ደግሞ ታላላቅ ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍና ሽኝት ሲደረግም ሚሊኒም አዳራሽ ላይ ነበር።
ይህ በኢትዮዽያ ግዙፉ አዳራሽ በሳለፍነው ሰኔ ወር 2017 ምሽት ላይ የተለመደውን አገልግሎት እየሰጠ በነበረበት ወቅት የእሳት አደጋ ያጋጠመው ሲሆን አሁን ሙሉ በሙሉ ተስተካክሎ ወደ ስራ መግባት ችሏል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕም ችግሩን በአጭር ጊዜ በመፍታት ወደ ስራ እንዲገባ አድርጎታል።
የችግሩ ምንጭ ለጊዜው በሚመለከተው አካል እየተጣራ በመሆኑ ጊዜው ሲደርስ ይፋ የሚደረግ ይሆናል።
ከዚህ በተጨማሪም ታህሳስ ወር 2018 ጀምሮ ሚሊኒየም አዳራሽ እጅግ ዘመናዊ በሆነ መልኩና አሁን ከሚሰጠው አገልግሎት በላቀ ደረጃ እንዲሰጥ ታስቦ እንደ አዲስ የሚገነባ ይሆናል።