14/12/2020
#ጃክ #ማ ጃክ ማ የቻይና የባህል አብዮት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት ድሃ ቤተሰብ ውስጥ ተወለደ ፡፡ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለ ነበር የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታውን ለማሻሻል ብቻ ቱሪስቶችን በነፃ ያስጎበኝ የነበረው ፡፡ ትምህርቱንም ካጠናቀቀ በኋላ ጃክ ማ ድህነትን ማስወገጃ ብቸኛው መንገድ ትምህርት ነው የሚል አስተሳሰብ ስለነበረው ለተለያዩ ኮሌጆች ለቀጣይ ትምህርት ማመልከት ጀመረ ፣ ሆኖም ግን በሁሉም ተቀባይነትን አጣ ፡፡ በቀጣይም ለ ሰላሳ የተለያዩ ሥራዎች ካመለከተ በኋላ ያገኘው መልስ ሁሉ በ ሁለት ቀላል ቃላት ይጠቃለል ነበር።ይህም “ብቁ አይደለህም” በሚሉ ሁለት ቀላል ለእርሱ ግን ቅስም ሰባሪ መዶሻ ቃላት ነበር ፡፡ KFC ሥራ ለማግኘት አብረዉት ካመለከቱ ከ 24 ሰዎች መካከል በድርጅቱ ተቀባይነትን ያላገኘው እሱ ብቻ ነበር ፡፡
በ 1995 (እ.ኤ.አ.) በይነመረብ እጅግ ያበበበት ዘመን ነበር። በዚህ ወቅት ነው እንግዲህ ጃክማ አንድ ነገር እጅግ ትኩረቱን የሳበው። ይህም ከበይነመረብ ገበታ “ቢራ” ን ከቻይና ሲፈልግ ምንም አይነት ውጤት ባለመገኘቱ ደነገጠ ፡፡እንዴት ቻይናን የሚያክል ሰፊ ሃገር ከበይነመረብ የዚህን ያህል ትርቃለች? በአሜሪካን አገር ቆይታው በዚያ የነበሩ በርካታ የበይነመረብ የንግድ ተቋማትን ተመልክቶ በአገሩ ቻይና ደግሞ አንድ እንኳን እዚህ ግባ ሊባል የሚችል የበይነመረብ የንግድ ተቋም አለመኖሩ አስገርሞታል። ጃክ ማ እንደ ብዙዎቻችን በዚህ ጉዳይ ተገርሞ ሲቀጥልም በቁጭት ወይም አገሩን በማማረር እድሜውን መፍጀት አልፈለገም። ነገር ግን ይህን ችግር እንደ ትልቅ አጋጣሚ በመመልከት የራሱንና የአገሩን ታሪክ የሚቀይርበትን ቀመር ፍለጋ ይኳትን ጀመር። በዚህ ወርቃማ ጊዜ ነበር እንግዲህ አሊባባን የመመስረት አይኑ የተከፈተው። ወደ አገሩ ቻይና ተመልሶ በመኖሪያ ቤቱ አሊባባን አቋቋመ።ምንም አይነት የበየነመረብ መሰረተ ልማት በሌለበት በቻይና ምድር የኢ-ኮሜርስ ድርጅት ለማቋቋም መሯሯጥ በአብዛኞቻችን የማህበረሰብ አካላት ዘንዳ እንደምናስበው እብደት ነበር የሚመስልው። በዚህም “ጃክማ አብዷል ኢንተርኔት እያለ የማይሰራ ነገር ያወራል” ይሉት እንደነበር እራሱ ጃክ ማ ይናገራል። እርሱ ግን በውስጡ ታላቅ ተስፋን ሰንቋልና በማንም ወሬ ሳይበገር ትግሉን ቀጠለ። ነገር ግን ይህ ትግል ለ ሶስት አመታት ያላንዳች ገቢ የቆየ በመሆኑ እጅግ ፈታኝና ተስፋ አስቆራጭም ነበር። ጃክ ማ ስራውን ጀምሮ ለ ሶስት አመታት ያህል አገልግሎት ይሰጥ የነበረው በነጻ ነበር።
በኋላም አስራ ሰባቱ ጓደኞቹን በራዕዩ ላይ ኢንቬስት እንዲያደርጉ ጠየቀ ፣ ምክንያቱም እሱ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም በሀሳቡ ይተማመን ስለነበር ነው። በነጻ ሲያገለግላቸው የነበሩ ደንበኞች እንዲህ ይሉት ነበር “ጃክ አንተኮ ምንም ትርፍ እንደማታገኝ እናውቃለን በጣም እናመሰግናለን” ይሉት ነበር። ጃክማ ይህን ሲገልጽ “ይህ ለእኔ ከገንዘብ በላይ ተስፋና አቅም ሆነኝ” ይላል። ምክንያቱም ይላል ጃክ ማ ሲናገር “ደንበኛህ ደስተኛ ከሆነ በቃ አንተ ተሳክቶልሃል። ዛሬ በነጻ ያገለገልከው ደንበኛህ ደስተኛ ከሆነ የነገ የገንዘብ ምንጭህ ነው።
ጃክ ማ እንዳለውም ብዙም ሳይቆይ ድርጅቱ ገንዘብ ማስገኘት ጀመረ።
በመጨረሻም አሊባባን አለማችን ላይ ከሚገኙ ታላላቅ የኢ-ኮሜርስ ድህረ-ገጾች አንዱ ሆነ። ፎርቢስ እንዳስነበበን ዛሬ ላይ ጃክ ማ የ 65.6 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ባለቤት ነው። የጃክ ማ ታሪክ ብዙ ያስተምረናል፥ በራስዎ ለማመን እና ተስፋን ላለማጣት መቼም ቢሆን ወደ ኋላ አይበሉ የስኬት ምስጥሩ እዛ ውስጥ ይገኛልና።