07/10/2022
አለም አቀፍ የሳይበር ወር እና ታሪካዊ ዳራዉ
አለም አቀፍ የሳይበር ወር በወርሃ ጥቅምት በአለምአቀፍ ደረጃ ስለ ሳይበር ደህንነት ግንዛቤን ከፍ ለማድረግ ታስቦ የሚካሄድ የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ የንቅናቄ መርሃ ግብር ነዉ፡፡
የሳይበር ደህንነት ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ በ2004 እ.ኤ.አ የዜጎችን የሳይበር እዉቀት ለመጨመርና ንቃተ ህሊናቸዉን ከፍ በማድረግ ደህንነቱ የተጠበቀ የሳይበር አጠቃቀምን እንዲተገብሩ ታስቦ መከበር ጀመረ፡፡
ቀስ በቀስ በአዉሮፓ እና ሌሎች የአለም ሀገራት ተቀባይነቱ እየጨመረ መጥቶ፤ ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥሎ በአዉሮፓ ሀገራት ከ2012 እ.ኤ.አ. ጀምሮ መከበር ጀምሯል፡፡
የተለያዩ ሀገራት ይህን ፕሮግራም ሙሉ ወሩን አልያም ከወሩ ሳምንትን መርጠዉ እንደሚያከብሩት መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
አዉስትራሊያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለምሳሌ ጋና፣ሳዉዝ አፍሪካ፣ ሞሪሽየስ፣ ኢስዋቲኒ፣ጋምቢያና ሩዋንዳን ጨምሮ ሙሉ ወሩን ባይሆንም ከጥቅምት ወር አንዱን ሳምንት መርጠዉ እንደሚያከብሩት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ በ2012 ዓ/ም የመጀመሪያዉን ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር በሳምንት ደረጃ በጥቅምት ወር የመጨረሻው ሳምንት “ትኩረት ለሳይበር ደህንነት” በሚል መሪ ቃል የተለያዩ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና መርሃ ግብሮችን በማካሄድ ማክበር ጀምራለች፡፡
በ2014 ዓ.ም ደግሞ “የሳይበር ደህንነት የጋራ ሃላፊነት፤ እንወቅ፤ እንጠንቀቅ” በሚል መሪ ቃል 2ኛዉን የሳይበር ደህንነት ንቅናቄ በወር ደረጃ ከ ጥቅምት 1 ቀን እስከ 30 በተሳካ ሁኔታ ለአንድ ወር ያክል በኮንፈረንስ፣ በስልጠና ብሎም በተለያዩ የሚዲያ አውታረ መረቦች ንቅናቄዎች ተካሂደዉ ነበር፡፡
3ተኛዉ የሳይበር ወርም እንዲሁ በጥቅምት 2015 አ.ም በተሳካ ሁኔታ ይከበራል፤ የወሩ አላማወች እና ዝርዝር አላማዎችም የሚከተሉት ናቸዉ
የወሩ ግብ
የሳይበር ማህበረሰቡንና የተቋማትን የሳይበር ደህንነት ንቃተ-ህሊና ለማጎልበት የሚያስችል ንቅናቄን በማካሄድ የሃገራችንን የብሄራዊ ጥቅሞችን የማስጠበቅ ተልዕኮን ማገዝ ነዉ፡፡
የወሩ ዝርዝር አላማዎች
• የተቋማትን የሳይበር ደህንነት ጥቃት ተጋላጭነት ለማሻሻል
• የግሉ ዘርፍ የሳይበር ደህንነትን በማስጠበቅ የሚኖረዉን አስተዋዕፆ ማሳደግ
• የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ የሚያስችል የሰዉ ሃብት ልማት ላይ ንቅናቄ መፍጠር ነዉ፡፡
• የማህበረሰቡን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ የሚያሳድግ ንቅናቄ መፍጠር