21/11/2025
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ባለ 28 ገፁን የትራምፕ የሰላም እቅድ መረከባቸውን አስታወቁ፡፡ የዩክሬይኑ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ አዲሱን የአሜሪካ መንግስት የሰላም እቅድ ረቂቅ መረከባቸውን ገልፀዋል፡፡ 28 ገፆች ባሉት በዚህ ረቂቅ ላይ የመስማማትም ሆነ የተቃውሞ አስተያየት ያልሰጡት ዘለንስኪ በጉዳዩ ላይ በሚቀጥሉት ቀናት ከትራምፕ ጋር በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ማቀዳቸውን አስረድተዋል፡፡ በደፈናው ‹‹ማንኛውም ስምምነት የዩክሬይንን ሉአላዊነት የሚያከብር መሆን ይገባዋል›› ብለዋል፡፡
ይሁንና ኤኤፍፒ ይህንን ባለ28 ገፅ ረቂቅ ሰነድ እንደተመለከተው ገልፆ በረቂቁ ውስጥ ዩክሬይን በምስራቃዊ ክፍል የሚገኙ ግዛቶቿን ለሩሲያ እንድታስረክብ የሚገልፅ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በእቅዱ መሰረት ሉጋንስክና ዶኔስክ የተሰኙትን ግዛቶች ዩክሬይን ሙሉ በሙሉ ለቃ የመውጣት ግዴታ ያለባት ሲሆን እነዚህን ሁለት ግዛቶችና ክሬሚያን አሜሪካ የሩሲያ ግዛት ለመሆናቸው እውቅና እንደምትሰጥ የሚያሳይ ነው፡፡
እንዲሁም ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ መሆን የሚገባቸው የዩክሬይን ግዛቶች እንደሚኖሩም ይገልፃል፡፡ በሌላ በኩል ዩክሬይን በተደጋጋሚ የምትጠይቀውን የደህንነት ዋስትና በተመለከተ ይህ ረቂቅ አዲስ የመፍትሄ ሀሳብ ይዞ የቀረበ ነው፡፡ ዩክሬይን የአውሮፓ ወታደሮች በሰላም አስከባሪነት በአገሯ ውስጥ እንዲሰማሩ የጠየቀች ቢሆንም የትራምፕ ረቂቅ ግን ይህንን ተስፋዋን አጨልሞታል፡፡ ዩክሬይን የኔቶ አባል ባለመሆኗም የኔቶ ወታደሮች በአገሯ ውስጥ መሰማራት እንደማይችሉ የሚገልፀው ይህ ረቂቅ ጨምሮም ‹‹የአውሮፓ የጦር አውሮፕላኖች ለዩክሬይን የደህንነት ዋስትና ለመስጠት በፖላንድ ይሰፍራሉ›› ይላል፡፡ እንደዘገባው በእቅዱ መሰረት ዩክሬይን ያላትን የወታደሮች ቁጥር በግማሽ መቀነስ ይኖርባታል፡፡ እንዲሁም በ100 ቀናት ውስጥ በዩክሬይን ውስጥ አጠቃላይ ምርጫ መደረግ እንዳለበት የሚያሳስብ ረቂቅ ነው፡፡
በሌላ በኩል ሩሲያ በዚህ እቅድ ላይ ከተስማማች ወደአለም አቀፉ ኢኮኖሚ እንድትመለስ የሚደረግ ሲሆን የተጣለባት ማእቀብም ይነሳል፡፡ ክሬሚያን በጠቀለለችበት ወቅት ከተባረረችበት የቡድን 8 አባልነት መልሳ የምትገባ ሲሆን በድጋሚ በዩክሬይን ላይ ወረራ ከፈፀመች ማእቀቡ ተመልሶ እንደሚጣልባት የሚያሳይ እቅድ ነው፡፡ አንድ የዩክሬይን ባለስልጣን ከዜና ምንጩ ሲናገሩ ‹‹ይህንን እቅድ አውጥተው ለአሜሪካ የሰጡት ሩሲያዊያን ናቸው›› ያሉ ሲሆን ኋይት ሀውስ ግን ይህንን አስተባብሏል፡፡ የኋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ካሮሊን ሌቪት ሲናገሩ ‹‹እቅዱን ፕሬዝደንት ትራምፕ ሙሉ በሙሉ የደገፉት ነው፡፡ ለዩክሬይንም ሆነ ለሩሲያ እንዲጠቅም አድርገን ያዘጋጀነው ነው›› ብለዋል፡፡