17/09/2026
"ዘላቂ ሠላም እንዲሠፍን የሴቶች ሚና ትልቅ ነው"
አቶ መሠለ ጫካ
#መስከረም 07/2019 እንሴኖ
"እኔ የሠላም እናት ነኝ" በሚል መሪ ቃል የምስራቅ ጉራጌ ዞን የምስራቅ መስቃን ወረዳ እና የእንሴኖ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት እንዲሁም የማረቆ ልዩ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት በጋራ በሁለቱ እህትና ወንድም ህዝቦች መካከል የተፈጠረውን ግጭት በማስቀረት ወደ ቀደመው መልካም ግንኙነት ለመመለስ ያለመ የጋራ የሠላም ኮንፍረንስ አካሄደዋል።
በክልላችን ርዕሰ መሥተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት፤ በምስራቅ ጉራጌ ዞን በምስራቅ መስቃን ወረዳ እንሴኖ ከተማ አስተዳደር እና በማረቆ ልዩ ወረዳ እናቶች የጋራ መድረክ ሰለሠላም ፓናል ውይይት፣ ለሠላም ለመስራት ቃል የመግባትና አብሮነትን በሚያጠናክሩ ልዩ ልዩ ሁነቶች የጋራ የሠላም ኮንፍረንሱ ደምቆ ውሏል።
የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪና የዞኑ ብልፅግና ፓርት ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሠለ ጫካ በጋራ የሰላም ከንፍረሱ ላይ እንደተናገሩት ዘላቂ ሠላም እንዲሠፍን የሴቶች ሚና ትልቅ መሆኑን በመግለፅ እናቶች ቤተሠብ ይገነባሉ ወጣ ያለን ይገስፃሉ፣ ያስተካክላሉ ትጥቅ እንኳን ማስፈታት የሚችሉ የሠላም መሠረቶች ናቸው ብለዋል።
ቆጥረን የማንደርሰው የጋራ መልካም ግንኙነት እያሉን መጥፎ መጥፎን እየነገሩ ለብዙ ወገኖቻችን ሞትና መፈናቀል ምክንያት እየሆነ ያለው ግጭት እናቶች ያላችሁን ትልቅ ሚና በማህበራዊ አደረጃጀቱ፤ ቡና ስትጠጡ፣ በየገበያው በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለሠላም እንዲሠሩ የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
መንግስት የተፈጠረው ግጭት እንዲፈታ እርቅ እንዲሠፍን የተጎዳ እንዲካስ ያዘነ እንዲፅናና የተፈናቀለውም ወደየቀየው እንዲመለስ በማድረግ የነበረው አብሮነት እንዲቀጥል እንደሚሠራ ገልፀዋል።
ለህዝብ ሠላምና ለአብሮነት አደጋ የሆኑ አካላት ህግን መሠረት ያደረገ እርምጃ ለመውሰድ መንግስት ሁልጊዜም ዝግጁ ቢሆንም በማሰር ሳይሆን በመምከር መመለስን ቅድሚያ እንደሚሠጥ ታውቆ እናቶችና በአጠቃላይ ማህበሰቡ ለዘላቂ ሠላም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የማረቆ ልዩ ወረዳ ዋና የመንግስት ተጠሪና የብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ እንዳሻው ግዛው በበኩላቸው በ2ቱ ወንድምና እህት ህዝቦች መካከል የተፈጠረውን ችግር በመቅረፍ የትኛውም የማህበረሰብ አካላት ያለምንም ስጋት እንዲኖርና ተንቀሳቅሶ መስራት እንዲችል አጠናክረን እንሰራለን ነው ያሉት።
በእጃችን ያለው የሠላም ዕድል በአግባቡ በመገንዘብ በመካክላችን ያሉ ችግር ፈጣሪዎችን መንጥረን በማውጣት ቀጠናችን የሠላም ተምሳሌት እናደርጋታለን ብለዋል።
የምስራቅ ጉራጌ ዞን ሴቶችና ህፃናት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ረሂማ ሰኢድ በመድረኩ እንደተናገሩት "እኔ የሠላም እናት ነኝ" በሚል መሪ ቃል የጋራ የሠላም ኮንፍረንስ በሚል በሁለቱ አዋሳኝ ህዝቦች መካከል የተፈጠረው ችግር እንዲፈታ ግንኝነታችን ለማሻሻልና የነበረውን አብሮነት ለማስቀጠል የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን አስታውቀዋል።
እለት ተዕለት ለልጆቿና ለቤተሰቦቿ የዕለት ጉርስ ለማሟላት ደፋ ቀና እያሉ ያሉ እናቶችን በፅንፈኛው ሀይል የሚሞትበት ሁኔታን በጋራ በቃ ልንለውና ልናወግዘው ይገባል ብለዋል።
ሁላችንም የሠላም እናቶች የሠላም ሀዋሪያ ሆነን በውስጣች ያሉ አዋኪ ኃይሎችን ሳንሸሽግ የወንድሞች አባቶች፣ የእናቶችና ህፃናት ሞት እንዲቆም በጋራ መስራት እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
የማረቆ ልዩ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ጽ/ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ማርታ ተሠማ በበኩላቸው በኮንፍረንሱ ኦንደተናገሩት ባለፉት ጊዜያት በተፈጠረው ግጭት ሞትና መፈናቀል ያስተናገድንበት ችግር በጋራ አውግዘን ለመፍትሔ የጋራ መድረክ መፈጠሩ እንዳስደሠታቸው ገልፀዋል።
እኛ ሴቶች ተቀራርበን ከሰራን ሰላም ማስፈን እንደምንችል በመረዳት በቀጣይም በተጠናከረ መልኩ በመስራት ወደሚፈለገው አብሮነትና ፍፁም ሠላም መስፍን የድርሻችንን መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በምስራቅ ጉራጌ ዞን የእንሴኖ ከተማ ዋና ከንቲባ አቶ መሀመድ ሠርሞሎ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው እንዳሉት በቀጠናችን ላይ የተፈጠረውን ግጭት ለመቅረፍ በተሠራው ሥራ የሠፈነው አንፃራዊ ሠላም ወደ ዘላቂ ሰላም ማሻገር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
እያንዳንዱ ነዋሪ የተፈጠሩትን ችግሮች የኔ ችግር ነው ብሎ በመውሰድ ለመፍትሔው ተቀራርቦ በመሥራት ለሠላም በመትጋት ነጣጣይ ትርክቶችን በመተው የቆየው አብሮነት እንዲታደስ ሴቶች እንዲሰሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በጨረሻም በእንሴኖ ከተማ ጎዳናዎች ሠላማዊ የእግር ጉዞ በማድረግና በልዩ ልዩ ሁነቶች ደምቆ የዕለቱ የጋራ የሠላም ኮንፈረንስ መድረኩ ተጠናቋል።