16/02/2024
በየጦር ግንባሩ እየተመታና እተሳደደ ያለው ፅንፈኛ ኃይል የጥፋት ስራውን መልክ እቀያየረ ይኸውና አሁን አሁን በዜጋችን ላይ ከፍተኛ ግፍና በደል እየፈፀመ ይገኛል፡፡ በተለይ ዜጎችን በማገት ከፍተኛ ገንዘብ ይሠበስባል፤ የዕለት ተዕለት ውሎን በማስተጓጎል በህዝብ ላይ ከፍተኛ ስጋት በመፈፀም ላይም ይገኛል፡፡ በዚህ የተማረረው የክልሉ ነዋሪ ነጋዴ በተለይ የስራ እድል የሚፈጥረው እና ኑሮን የሚያረጋጋው ነጋዴ በስጋት እና በምሬት አካባቢውን ጥሎ መሰደድ ጀምሯል፡፡ እንዲህ አይነቱን እኩይ ተግባር እየፈፀመና እያስተባበረ ያለው ይሄው ዘራፊ እና የማፍያ ቡድን ነው፡፡
ከህዝብ የመጣውን ምሬትና እሮሮ የከተማ አመራሩ ገምግሞ አቅጣጫ በማስቀመጥ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡ በዚህም በባህርዳር ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች የቤት ለቤት ፍተሻ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በዚህ ሂደት በተደረገው የቤት ለቤት ፍተሸ ከተገኙት መሳሪያ እና ተተኳሽ ውስጥ ብሬን2፣ ስናይፐር 1፣ ክላሽ 7፣ የተለያዩ ሽጉጦች 72፣ የሽጉጥ ጥይቶች 10223፣ የብሬን ጥይት 2406፣ 4 ቦምብ ፣ ዘጠኝ አጋቾች ከሚጠቀሙበት ተሸከርካሪ ጋር ተይዘዋል፡፡ ሁለት አጋቾች ደግሞ ካገቱ በኃላ 1.7 ሚሊዮን ብር ሲቀበሉ ተይዘዋል፡፡ አንድ የባንክ ሰራተኛ የግለሰቦችን አካውንት እያየ ለአጋቾች መረጃ እንደሚሰጥ ተደርሶበት በጥርጣሬ ተይዟል፡፡ በግድያና በተለያዩ ወንጀሎች ከተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች መጥተው የተደበቁ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወንጀለኞችም ተይዘዋል፡፡ ከከተሞችና ከገጠር ወረዳ (ከሜጫ ወረዳ እና መራዊ ከተማ) የተዘረፉ የህዝብ ሀብቶች በፍተሻ ተይዘዋል፡፡ ዘራፊዎች ማን ከማን ጋር እንደሚገናኙ አስፈላጊው መረጃ ተገኝቶበታል፡፡
እነዚህ ተግባራት በህብረተሰቡ ተሳትፎ በመሰራታቸው ዘራፊው ሀይል መሽጎ ከተቀመጠበት እግሬ አውጭኝ በማለት በመሸሽ ላይ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል የዘራፊው ሀይል ስምሪት ሰጭና አዛዥ የሆነው ፅንፈኛው ሚዲያ ይህንን ትግል ለማኮላሸት ዘረፋ ተካሄደ በሚል የተለመደ ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳውን በመንዛት ላይ ይገኛል፡፡ ነገር ግን አፈፃፀሙ ህጋዊ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ምንም ተፅዕኖ ሳይደርስባቸው በኮሚቴ ለሚንቀሳቀሱ ፈታሾች ፈቃዳቸውን በማሳየት ታልፈዋል፡፡ሂደቱም እጅግ በጥንቃቄ እየተመራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ገልጿል፡፡ እስከ አሁን የቀረበ አቤቱታ ባይኖርም የሚመጣ ቅሬታ እና አቤቱታ ካለም መንግስት ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡
በዚህም ምክንያት መላው የከተማው ሰላም ወዳድ ማህበረሰብ ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመጠየቅና በመተባበር የእገሌ ቤት ታልፏል፣ በደንብ አልተፈተሸም በማለት እየተባበረ እና መረጃ እየሰጠ ይገኛል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ሰላም ወዳድ ህዝብም ምስጋናውን በማቅረብ ይህ የተጀመረ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ለነዋሪው ህብረተሰብ አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጧል፡፡