18/09/2019
ፋብሪካው በቀጣይ ዓመት በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነ ሚስጥራዊ ኅትመት ሊጀምር ነው፡፡
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 28/2011 ዓ.ም (አብመድ) የዓባይ ኅትመት እና የወረቀት ፓኬጂንግ ፋብሪካ በአማራ ክልል የነበረውን የኅትመት ችግር እንደቀረፈ ተገልጧል፡፡
ዓባይ ኅትመት እና የወረቀት ፓኬጂንግ ፋብሪካ ሀምሌ 2010 ዓ.ም ነበር ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው። የተቋቋመውም በአማራ አቀፍ ልማት ማኅበር እና በአማራ ክልል ደን ኢንተርፕራይዝ አማካኝነት ነው፡፡ ፋብሪካው በ2011 በጀት ዓመት ደግሞ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ በሥራ ላይ በቆየባቸው ጊዜያትም ከ1ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የመማሪያ መጻህፍትን በክልሉ በሚነገሩ በሁሉም ቋንቋዎች አሳትሞ ለክልሉ ትምህርት ቢሮ እንዳስረከበ የፋብሪካዉ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ታደሰ መላሽ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ በሺህዎች የሚቆጠሩ የልቦለድ መፅሐፍት እና የበኩር ጋዜጣ ሳምንታዊ ህትመቶችን፣ የልማት ድርጅቶች ማስታወቂያዎችን፣ የአብቁተ የደበኞች የቁጠባ ደብተሮችን እና ሌሎች ኅትመቶችን በተሻለ ደረጃ ማሳተማቸውንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
በዚህም ከ73 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ብር የሚያወጣ የኅትመት ሥራ እንደሰሩ ነው የገለጹት፡፡ አዲሱ የፍኖተ ካርታ ወደ ተግባር ከገባ የተሻለ ሥራ ሊኖር እንደሚችል የተናሩት አቶ ታደሰ የክልሉ መንግስት በቀጣይ ዓመት እዲታተሙለት ከሚፈልጋቸው ውስጥ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን መማሪያ መፅሐፍት በጨረታ አሸንፈው እየሰሩ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ፋብሪካው በቋሚ እና በጊዜያዊነት ለ 175 ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል፡፡ ከአንድ ፈረቃ በላይ ወደ መሥራት ሲሸጋገር የስራ እድል የሚፈጠርላቸው ዜጎች በጥፍ ሊጨምር እንደሚችልም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ በቀጣይ ዓመትም በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነ ሚስጥራዊ የኅትመት ሥራዎችን ሊጀምር ከውጭ ኩባንያ ጋር ስምምነት ላይ እንደደረሰ ታውቋል፡፡ የሚስጥራዊ ኅትመት ማሽኑ የትምህርት ማስረጃ፣ ቼክ፣ የቦታ ባለቤትነት ማረጋጋጫ እና ሌሎች ግለሰባዊ ሰነዶችን የሚያትም ነው፡፡ ይህም ሀሰተኛ ኅትመቶችን ይከላከላል፡፡
የመብራት መቆራረጥ፣ የጥሬ እቃ አቅርቦት በተለይም ወረቀት የመጀመሪያ እትም መፈለጉ እና ድጋሜ የተሰሩ ወረቀቶችን ማሽኑ አለመጠቀሙ፣ ድርጅቱ ወደ ሥራ ሲገባ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ አለመኖር እና የውጭ ምንዛሬ ችግሮች ውጤታማነቱን እየተፈታተኑት እንደሆነ ታውቋል፡፡
የዓባይ ኅትመት እና የወረቀት ፓኬጅንግ ፋብሪካ ለክልሉ የመማሪያ መጽሐፍት እጥረትን በመቅረፍ እና እንግልቶችን በማስቀረት በኩል ምን ጠቀመ? ለአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለ ያቀረብንላቸው ጥያቄ ነው፡፡
እንደ ዶክተር ይልቃል መረጃ ፋብሪካዉ በክልሉ መከፈቱ መጻሕፍትን አዲስ አበባ ድረስ ሄዶ ከማሳተም ይልቅ በቅርብ አገልግሎቱን ለማግኘት አስችሏል፡፡ ይህም የጊዜ እና የገንዘብ ብክነትን አስቀርቷል፤ በቅርብ ተገኝቶ ማስተካከያ ለመስጠትም አመቺ ሆኗል፡፡
ፋብሪካው በመጻህፍት እና በጋዜጦች ኅትመት በሦስት ማሽኖች በእያንዳንዳቸው በሰዓት 35 ሺህ “ሺቶችን” ይሠራል፡፡ አንድ “ሺት” 16 ገጽ ነው፡፡ በሦስቱ ማሽኖች 105 ሺህ በሰዓት ማተም ይችላል እንደማለት ነው፡፡ የመጽሐፍ እና የመጽሄት ሽፋን የሚሰሩ ሁለት ማሽኖች ደግሞ እያንዳንዳቸው በሰዓት 13 ሺህ “ሺት” ያትማሉ፡፡
የመጽሐፍቱን ሁሉንም ሥራ የሚጨርሱ ሁለት ማሽኖችም እያንዳንዳቸው በሰዓት 6 ሺህ መጻፍቶችን አትመው ያጠናቅቃሉ፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ