25/12/2022
መጽሐፍ ቅዱስን በዮኒዚም ትርጓሜ ስንፈታቸው
***
ባሻዬ ናማ እስኪ
መጽሐፍ ቅዱስን ገለጥ ስታደርገው....አውን እጅህ ላይ ያለውን ስልሳ ስድስቱ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንባብ ስትከፍተው በሥጋ ንባብ አስደንጋጭ ነገር ግን በሃቅ እና በመንፈስ ሚዛን ላይ ትክክል የሆኑ እንዲህ አይነት ቃላትን ታገኛለህ።
***
“ዲቃላ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ፤ እስከ አሥር ትውልድ ድረስ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ።....ዘዳ23፥2"
ይህን ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሳይሆን ገድለ መርቆርዮስ ወይም ገደለ ተክለሃይማኖት ላይ ተገኝቶ ቢሆንስ? የስንት ሳምንት ኦርቶዶክሱን የመስደብያ የስብከት እንጅራህ ይሆን ነበር?
+++
ሌላም እስኪ እንመልከት ...
“ለጥፋት ለቀረበው ሰው ብርቱ መጠጥ ስጡት፥ ነፍሱ ለመረረውም የወይን ጠጅ ስጡት፣ይጠጣ ድህነቱንም ይርሳ፥ ጕስቍልናውንም ከእንግዲህ ወዲህ አያስብ።...ምሳሌ 31፥6-7"
ይህ በጠቢቡ ስለምን እጅ በኩል የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ በኦርቶዶክስ አንደኛው የጸሎት፣የታምራት፣የገድላት መጽሐፍ ላይ ብታገኘውስ? ህዝቡ ሰካራም የሆነው እንዲህ አይነት የስካር መንፈስ የያዙ መጽሐፍትን እየተሻሹ ነው ... ኡ ኡ ። ይህ ጣዖት አምላኪነት ነው ትለን ነበር አ?
+++
ባሻዬ
እባብ አዳኝ ነው የሚል ሐሳብ ያለው ንባብ ላሳይህ እስኪ..
“ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ፤ እባብም የነደፈችው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ። ዘኍ21፥9" "
እባብ እያዪ ህዝቡ ዳኑ። ይህን ቃል በደንብ አድርገህ ደጋግመህ አንብበው ።
ይህ ቃል በታምረ ማርያም ላይ ቢኖርስ? እባብ አዳኝ የሆነበት የጥልቁ መንፈስ አሰራር ያለበት መቅደስ ውስጥ መኖር ጣዖት አምላኪነት ተብሎብን አዳራሽ ሙሉ መንጋ ይጮኸብን ነበር።ግን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብቻ ነው ያለው።
+++
“ደንቆሮዎች፥ ሉቃ11፥40//“ውሾች ፣ፊል 3፥2//“ጋለሞታ 1ኛ ቆሮ 6፥15// ወዘተ ተብለው የተጻፉ ቃላት ገድላት ላይ ቢገኙ,...
የዘንዶው የስድብ አፍ የተሰጣቸው ተብሎልን የ2 ወር የአዳራሽ ስብከት ማሞቂያ እንሆን ነበር
+++
ስለኢየሱስ በተጻፈው ሐሳብ ላይ
“በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም። ማቴ 10፥34"
የሚለው የወንጌል ልሳን ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ በአዋልድ መጽሐፍት ከሆኑት በአንዱ ላይ ቢኖርስ? የሰላሙን አለቃ ጠብ ጫሪ አደረጉት፣አዳኙን ገዳይ ነው አሉት፣ ተብሎልን በፍጩት እና በጩኸት በቀለጠ ኡኡታ ጆሯችን ይደማ ነበር።
+++
ስለኢየሱስ ክብር በሚያትተው የመጽሐፍ ክፍል ላይ
“ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስ... ዕብ 2፥9"
የሚለውን ሐሳብ ታምረ ማርያም ውስጥ ቢገኝ ምን አይነት ፉጩት እና ሁከት እንደሚፈጠር አስባችሁታል?
ኢየሱስን ከመላእክት አሳንሰው፣ክርስቶስን ከገብርኤል ከሚካኤል በታች አድርገው ተብሎ ሰማይ ሰንጣቂ ጩኸት ይሰማ ነበር።
+++
መርቆርዮስ ቀይ ባህርን ለሁለት ከፈለ፣ተክልዬ ጸሐይን በገባዖ አቆመ፣ቅዱስ ያሬድ ከእንስሳ ጋር ቃል በቃል አወራ፣ የሚሉ ሐሳቦች ገድላት ላይ ቢገኙ የምንዱባዮችን ጩኸት አስባቹታል...
ከፊደል ጋር በግርድፉ መጋጨት የመንፈስ ሞት ያስከትላል። እንኳን ገድላትን ይቅርና መጽሐፍ ቅዱስ በግርድፍ የቃል ዐረፍተ ነገር ልፍታው ብትል መገኛህ እንጦሮንጦስ ነው። ምክንያት ካልከኝ
“ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል።”
— 2ኛ ቆሮ 3፥6 የሚል የእግዚአብሔር ህግ ስላለ።
እግዚአብሔር ይመስገን !
Kune Demelash kassaye -Arba Minch