08/09/2026
የሰኞ ሰይፈ ሥላሴ (መቅድሙና የዘወትሩ ከበታች ተካቷል)
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በማመን በዕለተ ሰኑይ የሚጸለይ የሰይፈ ሥላሴ ጸሎት።
፩. ጥንትና ፍጻሜ የሌለበት ለዘለዓለም የሚኖር አምላካችን እግዚአብሔር ታላቅና ገናና ነው።
፪. አቤቱ ጌታዬ ሆይ፥ ከሚያሥፈራኝ ክፉ ነገር ሁሉ ታድነኝ ዘንድ እለምንሃለሁ እማልድሃለሁ የሰይጣንን ተንኮል ሁሉ ከእኔ አርቅ፤ አቤቱ ያዕቆብንና ልጆቹን እንደባረክህ እኔንና ልጆቼን ቤተሰቦቼንና ዘመዶቼንም ባርክ በቸርነትህ በሰጠኸኝ ሀብትና ንብረቴ ላይ ረድኤትህና በረከትህን አሳድር።
፫. ለአንተ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ኃይል መንግሥት ክብርና ምስጋና ይገባል ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ በእውነት።
፬. አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኜ ልዩ ሦስት በሚሆኑ በቅድስት ሥላሴ እየተማፀንኩ በዚች እናቴ በምትሆን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፊት ቁሜ ጠላቴን ሰይጣንን እክዳለሁ፤ ዳግም በዚህ ዓለም በወዲያኛውም ዓለም አምባ መጠጊያ የምትሆነኝ ማርያምን ምስክር አድርጌ ለዘላለሙ አወግዛለሁ።
፭. በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኜ ዕረፍት አደርጋለሁ (እተኛለሁ)።
፮. በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እነቃለሁ።
፯. በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እነሣለሁ።
፰. በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምናለሁ እማፀናለሁ።
፱. በስም ሦስት በመለኮት ግን አንድ አምላክ ብዬ እማፀናለሁ።
፲. በአካል ሦስት በመንግሥት ግን አንድ አምላክ ብዬ እማፀናለሁ።
፲፩. በገጽ ሦስት ፍጹም በሚሆን የባሕርይ አንድነት ግን አንድ አምላክ ብዬ እማፀናለሁ።
፲፪. በቀን ከሚወረወር ጦር፣ በሌሊት ከሚዘዋወር ልዩ ጠላት እድን ዘንድ በዚህ በመለኮታዊ አንድነት እማፀናለሁ።
፲፫. ከአንዱ አንጻር ወደ ሌላው አንጻር መዘዋወር የሌለበት በእግዚአብሔር የፊቱ ምዕዛረ ብርሃን ፊቴን አማትባለሁ።
፲፬. በሚመለከትበት አንፃር የሚያስደነግጥ የሚያንቀጠቅጥ በእግዚአብሔር የዓይኖቹ የብርሃን ነፀብራቅ ዓይኖቼን አማትባለሁ።
፲፭. የተናገረውን በሚያደርግ በእግዚአብሔር ብርሃናዊ አንደበት አንደበቴን አማትባለሁ።
፲፮. መልካሙን በሚያናግር ዕውቀትንና ጥበብን በሚገልጽ በእግዚአብሔር ምዕዛረ ከናፍር ከንፈሮቼን አማትባለሁ።
፲፯. ያለማቋረጥ ለእርሱ ምስጋና የሚገባው የሰውን ጸሎት የሚሰማ በእግዚአብሔር ምዕዛረ አዕዛን ጆሮቼን አማትባለሁ። (እከፍታለሁ)።
፲፰. ያለመዳሰስ ዓለምን በያዙ በእግዚአብሔር የእጆቹ ምዕዛር እጆቼን አማትባለሁ (እዘረጋለሁ)።
፲፱. ከቂም በቀል ንጹሕ በሆነ በእግዚአብሔር ምዕዛረ ልቡና ልቡናዬን አማትባለሁ።
፳. ከልዩ ሐሳብ ልዩ በሆነ በእግዚአብሔር ምዕዛረ ሕሊና ኅሊናዬን አማትባለሁ።
፳፩. የቆምኩበትን አካባቢ የሚያነዋውጹ በእግዚአብሔር የእግሮቹ ምዕዛረ እግሮቼን አማትባለሁ።
፳፪. በሰማይና ከዚያም በላይ ባሉ እንዲሁም በምድርና ከዚያም በታች ባሉ ዓለመ ዓለማት ሁሉ እሱ የመላ ነውና ቦታ ለማይወስነው በእግዚአብሔር ምዕዛረ አካል ሰውነቴን አማትባለሁ።
፳፫. ጥንት ፥ ፍጻሜ በማይኖርበት (በሌለበት) በእግዚአብሔር ምዕዛረ ዘመን ዘመኔን አማትባለሁ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን አሜን።
፳፬. የለመለመ የምሕረት ምንጭ ለሚሆን ለአብ ሰላምታ ይገባል።
፳፭. የለመለመ የሕይወት መገኛ ለሚሆን ለወልድ ሰላምታ ይገባል።
፳፮. የለመለመ የሕይወት መፍለቂያ የሚሆን ለመንፈስ ቅዱስ ሰላምታ ይገባል።
፳፯. ሦስት የምሕረት መፍሰሻ አንድ የይቅርታ ምንጭ።
፳፰. አስቦ የማድረግ ችሎታና ሥልጣን ላለው ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፳፱. ኃይል ገንዘቡ የሆነ ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፴. ዓለምን በቃሉ ለፈጠረ ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፴፩. ሰውን በአርአያውና በአምሣሉ ለፈጠረ ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፴፪. ይቅርታን እንደ እህል ለሚዘራ ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፴፫. የብልጽግና መገኛ ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፴፬. መጉደል የሌለበት የስጦታ ባሕር ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፴፭. የእውነት ፍርድ መገኛ ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፴፮. በመለኮታዊ ሥልጣኑ ነፍስን ከሥጋ በሚለይ ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፴፯. በጌትነቱ መብረቅ ለሚንጸባረቅ ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፴፰. ለማይነዋወፅ የሃይማኖት ዓምድ ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፴፱. መፍረስ የሌለበት የመድኃኒት አዳራሽ ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፵. የቤቱ ግድግዳ በእሳት ለተሠራ ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፵፩. ድንኳኑ የእሳት ነበልባል ማደሪያውም በብርሃን ለተከበበ ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፵፪. በጽርሐ አርያም ለሚኖር ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፵፫. ዙፋኑን በኪሩቤል ላይ ለዘረጋ ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፵፬. በግልጽ ለሚበቀል ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፵፭. ለሚያደኸይና ለሚያበለጽግ ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፵፮. ለሚያዋርድና ለሚያከብር ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፵፯. ለመግደልና ለማዳን ሥልጣን ላለው ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፵፰. ለሚቀሥፍና ይቅር ለሚል ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፵፱. ለሚተክልና እንዲበቅል ለሚያደርግ ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፶. ለሚያደርቅና ለሚያለመልም ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፶፩. ሁሉን ማድረግ ለሚችል ልዩ ሦስት ለሚሆን አምላክ ሰላምታ ይገባል።
፶፪. ይህን ለመሰለ ማለት በአንድነትና በሦትነት ለሚመለክ አምላክ በእውነት እሰግዳለሁ።
፶፫. አቤቱ በዘመኑ ሁሉ የጥፋትና የኃጢአት አውሬ (ዲያብሎስ) እንዳይቀርበኝ በሐጹረ ቅዱስ መስቀልህ አጥርነት ጠብቀኝ አሜን።
፶፬-፶፭. አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ አንድ አመለካከት፤ ሦስት ገጽ አንድ መንግሥት፤ አንድ ፈቃድ ሦስት አካል አንድ ባሕርይ ነው።
፶፮. ሥላሴ ያለመከፋፈል በሦስትነት ያለ መጉደል በትክክል በአንዲት ፈቃድ በፍጹም አንድነት ይኖራሉ።
፶፯. ሦስትነት ከሰማየ ሰማያት ይልቅ ትመጥቃለች።
፶፰. ሦስትነት ከባሕሮች ጥልቀት ይልቅ ትጠልቃለች።
፶፱. ሥላሴ አኃዚተ ኵሉ ዓለማት ናት።
፷. ሦስትነት ከሰማያት በላይ ባሉ እና ከጥልቀቶችም ጥልቀት በታች ባሉ ሁሉ የመላች ናት።
፷፩. ሦስትነት በዓለም የስፋት አድማስና በማዕዘኗ ሁሉ ያለች ናት።
፷፪. ሦስትነት (ሥላሴ) የምሥራቆች ምሥራቅ የምዕራቦችም ምዕራብ ናት።
፷፫. ሥላሴ የሰሜኖች ሰሜን የደቡቦች ደቡብ ናት።
፷፬. ሥላሴን የሰፊዎች ሰፊ የሚሆን የቦታ ስፋት አይወስናትም።
፷፭. ሥላሴ (ሦስትነት) የንጋት ብርሃን መውጫ ናት።
፷፮. ሥላሴ በምሽት ጊዜ ጨለማን የምታሠለጥን ናት ።
፷፯. በዚህ የሥላሴ ስም ኃይል ከታላቅ አክብሮት ጋር ፍጹም የሆነ ይህን የሃይማኖትና የምስጋና ቃል ለቅድስት ሥላሴ በቀና አንደበት እዘምራለሁ።
፷፰. አምልኮና ስግደት መመለክና መስገድ ለቅድስት ሥላሴ ይገባል።
፷፱. ኃይል ጽንዕ መንግሥት ሥልጣንና ክሂል ለቅድስት ሥላሴ ይገባል።
፸. ጥበብና ምክር ጌትነትና ክብር ለቅድስት ሥላሴ ብቻ ይገባል።
፸፩. መግደል ማዳን መቅሠፍ ይቅርታ ማድረግ የቅድስት ሥላሴ ሥልጣን ነው።
፸፪. ማደኽየትና ማበልጸግ ማክበርና ማዋረድ የብቻ የቅድስት ሥላሴ ሥልጣን ነው።
፸፫. መትከል ማብቀል ማድረቅና ማለምለም የብቻ የቅድስት ሥላሴ ሥልጣን ነው።
፸፬. በምድርና በሰማይ በባሕርና በቀላያት ባሉ ፍጥረታት ሁሉ ላይ የገዥነት ሥልጣን ያለ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው።
፸፭. የመለኮትን አንድነት ገንዘብ በማድረግ ያለመለየትና ያለመከፋፈል በገጽ ሦስት በመለኮት አንድ ለሚሆን ለሱ ለብቻው መገዛት ይገባል።
፸፮. ለሱ ለብቻው ዘምሮ ለሱ ለብቻ ምስጋና ይገባል።
፸፯. እሱን እጅ መንሣት እሱን ማመስገን እሱን ማምለክ በእሱ መታመን ይገባል።
፸፰. እሱን መጠጋት ወደሱ መጸለይ በፊቱም መማለድ ይገባል።
፸፱· እሱ የአማልክቶች አምላክ የገዥዎች ገዥ የነገሥታት ንጉሥ ነው።
፹· አምላካችን የማዳን አምላክ ነው ሁሉን ማድረግ ይቻለዋል ለሱ የሚሳነው ነገር የለምና።
፹፩. ለመንግሥቱ መገዛት በመለኮቱም መታመንና መማፀን ይገባል።
፹፪. ልዩ ሦስት ሆይ እኔን በደለኛ የምሆን ባሪያችሁን ከድንገተኛ ሞት አድኑኝ አሜን።
፹፫. ቅድመ ዓለም የነበረ ለዘለዓለሙም የሚኖር ታላቅና ግሩም የሚሆን እንደ አምላካችን ያለ አምላክ ማን ነው።
፹፬. የአሕዛብ አምልኮታቸው ከወርቅና ከብር ከነሐስና ከመዳብ ከድንጋይና ከእንጨት ከኒኬልና ከሸክላ በሰው እጅ የተሠሩ ናቸው።
፹፭. አፍ እያላቸው አይናገሩም ዓይን እያላቸው አያዩም።
፹፮. ጆሮ እያላቸው አይሰሙም አፍንጫ እያላቸው አያሸቱም።
፹፯. እጅ እያላቸው አይዳስሱም እግር እያላቸው አይራመዱም ወይም አይሄዱም።
፹፰. በጉሮሮአቸው አይናገሩም በአፋቸው ውስጥ ትንፋሽ የላቸውም።
፹፱. እንግዲህ ሠሪዎቻቸውና የሚያምኑባቸው ሁሉ እንደ እነሱ ይሁኑ በእውነት ለዘላለሙ አሜን።
፺. ወልድ በሚከበርበት መንፈስ ቅዱስ በሚቀደስበት ገንዘብ በአብ የባሕርይ ስም አምናለሁ።
፺፩. አብ በሚወደስበት መንፈስ ቅዱስ በሚመሰገንበት ገንዘብ በወልድ የባሕርይ ስም አምናለሁ።
፺፪. አብ ከወልድ ጋር በአንድነት በሚመሰገንበት ገንዘብ በመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ ስም አምናለሁ።
፺፫. በዚህ በሥላሴ ስም እያመንኩ ጠላቴ ሰይጣንን እክዳለሁ አንተ እርኵስ መንፈስ ነህና።
፺፬. ልዩ ሦስት ሆይ እኔን ባሪያችሁን . . . ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ጠብቁኝ አድኑኝ ለዘላለሙ በእውነት።
ተአምር፦
፩. ይቅርታቸውና ሀብተ ረድኤታቸው ለአገልጋያቸው ይደረግለትና የሥላሴን ተአምራታቸው ይህ ነው።
፪. ጢሮዓዳ በሚበል አገር የፋርስ ንጉሥ ጭፍራ የሆነ አንድ ሰው ነበረ። ይህም ሰው ከዕለታት ባንድ ቀን የክርስቲያንን ሀገር ለማጥፋት ሰንጋ ፈረሱን ጭኖ ከቤቱ ወጣ።
፫. በዚህም አገር ውስጥ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ሥዕል ያለበት የተቀደሰ ቦታ ነበር።
፬. ከዚያም ንዋያተ ቅድሳቱን ለመመዝበር ወደ አማረውና ወደ ተጌጠው አዳራሽ በገባ ጊዜ የሥሉስ ቅዱስ ሥዕል ካለበት ቦታ ደረሰ።
፭. ይህም ወታደር የሥላሴን ሥዕል በእሳት ሰይፍ ታጥሮ ባየው ጊዜ በዚያ የነበሩትን ሰዎች ወንድሞቼ ሆይ ይህ እንደ ነደ እሳት የሚያንፀባርቅ ሥዕል ምንድን ነው አርአያው እጅግ አስፈራኝ ወደ እሱ ቀርቤም ሁኔታውን ለመረዳት ተሳነኝ አላቸው።
፮. እነዚያም የክርስቲያን ወገኖች አንተ ወታደር ፈጥነህ በምድር ላይ ወድቀህ ስገድ ይህ ስዕል የሥላሴ አርአያ ገጽ ነውና አሉት።
፯. በዚያን ጊዜ ፈጥኖ በጉልበቱ ተንበርክኮ ሰገደ እጁንም ወደ ሰማይ በመዘርጋት እኔ ለጌቶቼ ለሥላሴ ሥዕል እሰግዳለሁ እያለ ማለደ።
፰. ከአረማውያን ሀገር አውጥታችሁ ከክርስቲያኖች አገር አድርሳችሁኛልና ስለዚህም ምስጋና ላቀርብላችሁ እገደዳለሁ አለ።
፱. እንዲህም እያለ ሲጸልይ የእግዚአብሔር የጌትነቱ ብርሃን በዚያ ቤት ውስጥ መላ።
፲· በዚህም ጊዜ አንተ የንጉሥ ወታደር ሆይ መንግሥተ ሰማያት ትገባ ዘንድ ሥሉስ ቅዱስ ጠርተውሃል የሚል ቃል ከሰማይ መጣ።
፲፩. ይህንንም ከመስማቱ የእግዚአብሔር መልአክ መጋቤ ብርሃናት ራጉኤል በቅጽበት ወደሱ መጥቶ ወደ ሰማይ አሣረገውና በሥላሴ ፊት አቆመው።
፲፪. ሥላሴም ከሌሎቹ የንጉሥ ሠራዊት ተመርጠሽ ወደዚህ የመጣሽ ምርጥ ነፍስ ሆይ ወልድ በአባቱ ጌትነትና በመንፈስ ቅዱስ ክብር እስኪ መጣ ድረስ በሕያዋን አገር ገብተሽ በዚያ ትቀመጭ ዘንድ ፈቅደንልሻል አሏት።
፲፫. ይህንንም ካሏት በኋላ ወደዚያ አገር አስገቧትና በዚያ ተቀመጠች።
፲፬. ይቅርታቸውና ሀብተ ረድኤታቸው ከወዳጃቸው ጋር ለዘላለሙ ይኑር በእውነት አሜን።
***************
የሰይፈ ሥላሴ መቅድም
፩. ስቡሕ ወውዱስ እኩት ወቅዱስ እየተባለ በፍጹም ምስጋና የሚመሰገን፤ አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በማመን የሥላሴን ጥንተ ህልውና የሚናገር መጽሐፍ ለመጻፍ (ለመጸለይ) እንጀምራለን ።
፪. ነገር ግን እግዚአብሔር በሰጠን የችሎታ መጠን ለመናገር እንሞክራለን እንጂ ጽፈንስ ለመጨረስ፤ ችሎታ አይኖረንም።
፫. የምስጋናቸውንስ ነገር ሰማይና ምድር ወረቀት ወይም ብራና ቢሆኑ ከፍጥረተ ዓለም እስከ ኅልቀተ ዓለም ያለው ርደተ ዝናም ቀለም ቢሆን ይልቁንም ዓለም በጠቅላላው ለዚህ ተግባር ቢውል ተጽፎ የሚያልቅ አይደለም ለዘለዓለሙ በእውነት።
፬. ሰማይና ምድር ከመፈጠራቸው አስቀድሞ ሥላሴ በብቸኝነት ክብራቸው በአካል ሦስት በመለኮትና በፈቃድ በባሕርይ በትእዛዝ ግን አንዳችም ልዩነት ሣይኖርባቸው የነበሩ ናቸው ።
፭. አብ ያለወልድና ያለመንፈስ ቅዱስ ለአንዲት ሰዓት ስንኳ ብቻውን የነበረበት ጊዜ የለም።
፮. ወልድም ያለ አብና ያለ መንፈስ ቅዱስ ለአንዲት ደቂቃ ስንኳ ብቻውን የነበረበት ጊዜ የለም።
፯. መንፈስ ቅዱስም ያለ አብና ያለ ወልድ ለአንዲት ሰኮንድ ስንኳ ብቻውን የነበረበት ጊዜ የለም።
፰. ለአብ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ የተለየ ልዩ ፈቃድና እዘዝ የለውም።
፱. ለወልድም ከአብና ከመንፈሰ ቅዱስ የተለየ ልዩ ሥልጣንና ክሂል የለውም።
፲. ለመንፈስ ቅዱስም ከአብና ከወልድ የተለየ ምንም ዓይነት ሥልጣን የለውም።
፲፩. በማደህየትና በማበልፀግ በማዋረድና በማክበር ፍጹም ልዩነት የለባቸውም።
፲፪. በአንድነት በሦስትነት ይሰገዳሉ ይመለካሉ፤ ሁሉንም በየነገዱ በመፍጠር ትክክል ናቸው እንጂ ጉድለት ወይም ሕፀፅ ያሣዩበት ጊዜ የለም።
፲፫. እንደዚሁም ለአብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በአንድ ቃል ሰውን በአርአያችንና በምሳሌያችን እንፍጠር አሉ።
፲፬. እነሆ በመጀመሪያዪቱ ቀን በዕለተ እሑድ ስምንት ፍጥረታትን ማለት ሰማይንና ምድርን ጨለማንና ብርሃንን ነፋስንና እሳትን ውሀን መላእክትን ፈጥረው መላእክትን ግን በመቶ ነገድ ከፈሏቸው የመላእክትም ሁሉ አለቃቸው ሳጥናኤል (ዲያብሎስ) ነበረ።
፲፭. ከዚህ በኋላ መላእክትን በሙሉ ጨለማ ጋረዳቸው ሸፈናቸው።
፲፮. በዚህን ጊዜ መላእክት እርስ በራሳቸው ማን ፈጠረን ጌታችን ማነው በማንስ እናመልካለን ተባባሉ።
፲፯. ትምክህተኛው ወይም ሰይጣኑ መልአክም ይህን ቃል ሰምቶ ግራ ቀኝ ቢመለከት ከሌሎቹ የእርሱ ማዕርግ በልጦ ስለአገኘው እነሆ አምላካችሁና ፈጣሪያችሁ ገዥአችሁም እኔ ነኝ ሲል በድፍረት ተናገረ።
፲፰. ከዚህ በኋላ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከመከካላቸው ተነሥቶ ቆመና እናንት ማኅበረ መላእክት ሆይ፥ አምላካችንን እስክናውቅ ወይም እስክናገኘው ድረስ በእምነታችን ጸንተን መቆየት አለብን እንጂ በዚህ በሐሰተኛና በተንኮለኛ መልአክ አነጋገር ተወናብዳችሁ እንዳታምኑ ሲል በታላቅ ቃል አሰምቶ ተናገረ።
፲፱. በዚህም ጊዜ ኪሩቤልና ሱራፌል ዙፋኑን እንደ ተሸከሙ የሥላሴ ብርሃነ መለኮት ተገለጠ አንፀባረቀ በዓለሙ ሁሉ ላይም ብርሃን ይሁን አለ።
፳. ከዚህም በኋላ የዲያብሎስ የገዥነት ሥልጣኑ ተሽሮ እጅ እግሩን በእሳት ሠንሠለት ታሠረ።
፳፩. የተጐናጸፈውን ብርሃን ገፈው የጨለማ ጨርቅ አለበሱት የእሳት ነጐድጓድ አወረዱበት በልቡናው ፍርሃትን አሳደሩበት በዚህም ዘለዓለማዊው የሥላሴ መንግሥት በመላእክት ሁሉ ዘንድ ታወቀ ተረዳ።
፳፪. መላእክትንም ከነሱ ይለዩት ዘንድ አዘዝዋቸውና እነሱም ከመካከላቸው አውግዘው ለዩት።
፳፫. ሥሉስ ቅዱስም አንተ ርጉም ከኛ ራቅ መኖሪያህም በመንጸፈ ደይን ይሁን በማለት አስወገዱት።
፳፬. ይህ ርጉም መልአክም ጌቶቼ ከቶ ምሕረት የላችሁምን አላቸው።
፳፭. አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስም በእርግጥ አንተን ለመሰለ ሁሉ ምሕረት የለንም አሉት።
፳፮. በዚህ ጊዜ ይህ ርጉም መልአክ ጌቶቼ ሆይ፥ ከነዚህ ሁሉ የተፈጥሮ ጓደኞቼ ነገደ መላእክት ተለይቼ ስሄድ አላሳዝናችሁምን ሲል በማሳዘን ጮኾ ተናገረ።
፳፯. አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስም በማይቻልህ የአምላክነትን ባሕርይ ለመፈታተንና የማታልፈውን መንግሥታችንን ለመገልበጥ ያደረግኸው ሙከራና ድፍረት አያሳፍርህምን ይልቁንም በቃልህ አምነውበት አንተን የተከተሉ ሁሉ አብረውህ ከአንተ ጋር ይሂዱ አሉት።
፳፰. ቀጥሎም በልዩ አስተሳሰብህ አምላካዊ መንግሥትን ስትሻ ተገኝተሃልና መኖሪያህ ዕመቀ ዕመቃት ይሁን ቅዱስ ስማችን በተጠራበት ቦታ ሁሉ አትድረስ አሉት።
፳፱. ወገኖችህ መላእክት በጠላትነት ይነሱብህ በአለት ድንጋይ (ዕብነ ሩካም) በእሳት መንዶ እራስ እራስክን ይቀጥቅጡህ አሉት።
፴. ዳግመኛም ምግብህ የእሳት አሎሎ (ኮረት) መጠጥህ የእሳት ፍላት ይሁን መዘዋወሪያህ (መመላለሻህ) መንጸፈ ደይን ይሁን መቀመጫህ የእሳት መንኰራኵር ይሁን መኖሪያህም በጨለማ ውስጥ ይሁን ሲሉ ረገሙት።
፴፩. ይህንንም ካሉት በኋላ የቤቱ ዙሪያ በእሳት የታጠረ በውስጡም እሳት የሚነድበት ሆኖ ወደ ተዘጋጀለት ቤት በዚያ ይኖር ዘንድ ገባ ዕመቀ ዕመቃት መንጸፈ ደይን ወረደ።
፴፪. እሱ ግን በልቡ እግዚአብሔር እንደኔ ያለ ፍጡር አያገኝም ስለሆነም መልሶ እንደ ቀድሞው አገልጋዩ ያደርገኛል። ከቀድሞ የተፈጥሮ ጓደኞቼ ከሆኑ መላእክትም ሁሉ ጋራ ሥራዬን እቀጥላለሁ። ከአብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እተካከላለሁ። ለአብ ምስጋና አቀርባለሁ ከእሱም ጋር ነግሼ እኖራለሁ። ስለዚህም እርሱ አብ ያከብረኛል ወልድም ከአእላፍ መላእክቶቹ ጋር መጥቶ ይቀበለኛል። ከእሱም ጋር እኖራለሁ። የአብን የዙፋን መጋረጃ ገልጬ እገባና በቀኙ ያስቀምጠኛል። ከዚያም በሱ ላይ እሠለጥናለሁ። ከወልድ ራስ ላይ ዘውድን እነጥቃለሁ። ከመንፈስ ቅዱስም ላይ የብርሃን አክሊል ወስጄ እቀዳጅና ለዚያች ከማዕርጌ ላይ ያዋረደችኝና እጅግ አስፈሪ ለሆነችው ዙፋን ባለቤት እሆናለሁ።
፴፫. ከዚያም የቀድሞ ሥልጣኔን በእጄ ከአደረግሁ በኋላ ከኔ አፈንግጠው መመሪያየን ሳይቀበሉ የቀሩትንና በእኔ ሥልጣን ላይ የተቀመጡትን ጠላቶቼን ሁሉ በቁጥጥሬ ሥር አውላቸዋለሁ በማለት ታበየ።
፴፬. ይህንንም በልቡ ሐሳብ በሚልበት ጊዜ ይህ ዲያብሎስ ትሉ ወደ ማያንቀላፋበት ጢሱ እሳቱ ወደ ማይጠፋበት በሲኦል የረግረግ ጨለማ በድንገት ተወርውሮ ሰጠመ (ሠረገ)።
፴፭. እንደዚሁም ሁሉ ጠላቶቼ በሲኦል መካከል ባለ ጨለማ ውስጥ ይጣሉ እኔ አገልጋያችሁ . . . በእናንተ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ተማፅኛለሁና እስከ ዘላለሙ አሜን።
ሰይፈ ሥላሴ ዘዘወትር
፩. አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምናለሁ እማጸናለሁ።
፪. የዓለም ገዥ ሥሉስ ቅዱስ ሆይ፥ በወዳጃችሁ በአብርሃም ቤት እንደገባችሁ ከናንተ ዘንድ የሚሰጠውን የሰማዕትነት አክሊል እቀዳጅ ዘንድ ተድላ ደስታ ካለበት ገነት አግቡኝ።
፫. ኃጢአቴን በይቅርታ ቃል ደምስሳችሁ ነፍሴን ከሚቃወሟት አጋንንት አድኗት።
፬. አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሆይ፥ በእውነት ስማችሁን እጠራ ዘንድ ከወደቅሁበት አንሡኝ በቸርነታችሁም ከሩቅ ጥቀሱኝ ከቀትር ጋኔን ከድንገተኛ መጋኛ ትጠብቁኝ ዘንድ እማፀናለሁ።
፭. አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሆይ፥ የምስጋና ፍሬ እንዳፈራና ከአንደበቴም የጸሎት እሸት አበረክትላችሁ ዘንድ በልቡናዬ እርሻ ላይ መልካሙን ፍሬ ትዘሩ ዘንድ እማፀናለሁ።
፮. አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሆይ፥ ኃያሉ ስማችሁ የሚጋፉኝን ይጋፋቸው ዘንድ የሚቃወሙኝንም እንዲቃወማቸውና ፈርኦንን በነቢዩ በሙሴ ምክንያት እንዳሰጠመው ያሰጥማቸው ዘንድ በእናንተ እማፀናለሁ።
፯. አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሆይ፥ በአርያም ባለው ጽርሐ መንግሥታችሁ እማፀናለሁ ስለ ዕዝራና ሄኖክም ሲባል ገነትን ስለጐበኛችሁ እኔን ባሪያችሁን በቸርነታችሁ ጐብኙኝ።
፰. አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሆይ፥ በስማችሁ ብዙ ተአምራትን ያደረገና ኮከበ ክብር የተባለ የሰማዕታት አለቃ በሚሆን በኃያሉ በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ለመፍረድ በልዳ ሀገር የተሰበሰቡትን ፸ (ሰብዓ) ነገሥታትን ደምስሳችሁ እንዳጠፋችኋቸው የኔንም ጠላቶች ትደመስሱልኝ ዘንድ እማፀናለሁ።
፱. ጠላቶቾ የሆኑ ሁሉ በመለኮታዊ ሰይፍ ይ*ጨ*ፍ*ጨ*ፉ ነበልባላዊ በሚሆን ቃላችሁና ሥልጣናችሁ ይንደዱ ይቃጠሉ በሲኦል የጨለማ አዘቅት ውስጥ ይዝቀጡ ወይም ይስጠሙ ሐዘን ከላያቸው አይራቅ ትካዜም ከልባቸው አይጥፋ።
፲. ጠላቶቼ እኔ ከምድረ ገጽ ላይ እንድጠፋ በፈለጉ ጊዜ እነሱን ራሳቸውን እንደ ቃየልና ይሁዳ በዱርና በበረሃ በታትኗቸውና ሲቅበዘበዙ ይኑሩ።
፲፩. አዳምና ሔዋን ከገነት በመውጣታቸው እንዳለቀሱ ጠላቶቼንም የጨርቅ መቀነቻ አስታጥቋቸውና ሲያለቅሱ ይኑሩ።
፲፪. በኔም ላይ ጥፋትን እንዳያመጡብኝ ጥልቅ በሆነ በእሳት ባሕር አስጥሟቸው።
፲፫. አሁንም እነሆ ጠላቶቼ በእሾህና አሜካላ በተታታ ወጥመድ ውስጥ ይግቡ።
፲፬. ልዩ ሦስት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሆይ፥ ለእኔ ለባሪያችሁ ፍጹም ይቅርታን ታደርጉልኝ ዘንድ እማልዳለሁ።
፲፭. ጠላቶቼ ግን በፊታቸው ከፍርሃት በስተቀር በፍጹም ደስታን አያግኙ።
፲፮. ወንጀለኞች እንደሚታሠሩ እጅ እግራቸውን በእሳት ሠንሠለት እሠሯቸው እንጂ።
፲፯. ዳግመኛም ቀድሞ አዳም ከነ ልጆቹ በሲኦል ጨለማ እንደተከበበ እነሱንም የመከራ ጨለማ ይክበባቸው።
፲፰. ጠላቶቼን በውሾች ማደሪያ አሳድሯቸው የምታስፈራዋን ያችን የእሳት ባሕር አታሻግሯቸው።
፲፱. በእሳት ቀስት (ፍላፃ) ንደፏቸው ልዩ ልዩ ደዌና መቅሠፍት ይታዘዝባቸው የምሕረት ዝናም (ጠል) አይውረድላቸው የሕይወት ቃል አትመልሱላቸው።
፳. ልዩ ሦስት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሆይ፥ ጽንዕት በሆነች መለኮታዊት እጃችሁ ትባርኩኝና መላእክትም ሁሉ በክንፋቸው በእኔ ላይ ይረቡ ዘንድ እማፀናለሁ።
፳፩. ነፍሴ ወይም ሰውነቴ በእናንተ ዘንድ የተጠማች እንዳትሆን ከዐራቱ አፍላጋት በሚፈስ ውሀ አርኳት (አጠጧት)።
፳፪. ነፍሴ ወይም ሰውነቴ በፊታችሁ የተራበች ሆና እንዳትገኝ የሕይወት ኅብስት መግቧት።
፳፫. የነፍስና የሥጋ ገዥ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሆይ፥ የምስጋና ፍሬ አቀርብላችሁ ዘንድ ጾምና ጸሎት ወዳድ እንድታደርጉኝ እማጸናለሁ።
፳፬. ከነቢያትና ከሐዋርያት ጋር መኖሪያዬን በገነት አድርጉልኝ ከዕለት እኪት ከዘመን መንሱት ሠውሩኝ።
፳፭. እኔ በደለኛ የምሆን አገልጋያችሁ . . . ከድንገተኛ ሞት እድን ዘንድ ልዩ ሦስት በሚሆን ስማችሁ እማፀናለሁ ነፍሴንና ሥጋዬንም አደራ አስጠብቃለሁ። በዚያም ጊዜ ምሕረት ይደረግልኝ አሜን።
፳፮. ዳግመኛም በሁሉ ላይ ሥልጣን ባለው በእግዚአብሔር አብ ስም ዕውቀትን በሚገልጽ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እና ያዘኑትን በሚያረጋጋ እውነተኛ አዳኝ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ ስም እማፀናለሁ።
፳፯. በአካል ሦስት ሲሆን በመለኮት ግን አንድ አምላክ በሚሆን እማፀናለሁ።
፳፰. በየጊዜውና በየሰዓቱ እንግዳ ለሚሆንና ለማይጠገበው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ፍቅር እማፀናለሁ።
፳፱. በማይጠፋ በማያረጅና በማያልፍ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አነዋወር እማፀናለሁ።
፴. ተነግሮ በማያልቅ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ የጌትነት ምስጋና እማፀናለሁ።
፴፩. ዓለሙን ሁሉ ለይኩን ብሎ በአንዲት ቃል በፈጠረ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አምላካዊ ጥበብ እማፀናለሁ።
፴፪. በግልጽና በሥውር ያለውን ዓለም በሙሉ በአጸና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አምላካዊ ኃይል እማፀናለሁ።
፴፫. ለመግደልና ለማዳን በሚችል በአብና በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አምላካዊ ፍርድ እማፀናለሁ።
፴፬. ከምድረ ገጽ ጸብን ክርክርን በሚሽር በሚያጠፋና በሚደመስስ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አምላካዊ ቃል እማፀናለሁ።
፴፭. በሚያደኸይና በሚያበለጽግ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አምላካዊ መንግሥት ወይም ሥልጣን እማፀናለሁ።
፴፮. እጅግ በሚያስፈራና ነፍስና ሥጋን በሚያስደነግጥ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ግርማ እማፀናለሁ።
፴፯. ከአፉ በሚወጣ የእሳት ሰይፍ የጠላትን ወጥመድ (አሽክላ) የሚቆራርጥ በመለኮት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ እማፀናለሁ።
፴፰. አሌፍ፣ ቤት፣ ጋሜል፣ ዳሌጥ፣ ሄ፣ ዋው፣ ዛይ፣ ሔት፣ ጤት፣ ዮድ፣ ካፍ፣ ላሜድ፣ ሜም፣ ኖን፣ ሳምኬት፣ ዔ፣ ፌ፣ ጻዴ፣ ቆፍ፣ ሬስ፣ ሳን፣ ታው በሚባል (ሉ) በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያመንኩ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ልመናዬ ወዳንተ ትቀርብ ዘንድ እማፀናለሁ።
፴፱. የመምጣቱ ዜና በነቢያት አንደበት በተነገረና ከቅድስት ድንግል ማርያም በቤተልሔም በተወለደ ጌታ እማፀናለሁ።
፵. ዳግመኛም በማየ ዮርዳኖስ በተጠመቀውና የጌትነቱ ክብር በደብረ ታቦር በተገለጸው አምላክ እማፀናለሁ።
፵፩. ሀገሩ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ተብላ በምትጠራውና ማደሪያውን በአርያም መሠወሪያውንም የእሳት መጋረጃ ባደረገ በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እማፀናለሁ።
፵፪. በለበሰው ሥጋ በተሰቀለበት በመካነ ስቅለቱ በቀራንዮ በመካነ መቃብሩ በጎልጎታ ከሙታን ተለይቶ በሦስተኛው ቀን በመነሣቱ በዐርባኛው ቀን ወደ ሰማይ በማረጉና ይህን ዓለም ለማሳለፍ ዳግመኛ በመምጣቱ እማፀናለሁ።
፵፫. ለአዳምና ለልጆቹ ለዘሩም ሁሉ መድኃኒት ይሆን ዘንድ ከሰማይ በወረደ በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ እማፀናለሁ።
፵፬. በዚህ ሁሉ በተጠሩትና ባልተጠሩት አምላካዊና የመማፀኛ ስሞች እናንት ርኵሳን አጋንንት እኵያንና መሠርያን ሰብዓዊ ፍጥረቶች ሁሉ በየጊዜውና በየሰዓቱ የእግዚአብሔር አገልጋዩ ከምሆን ከኔ ዘንድ እንዳትቀርቡ የተወገዛችሁ ሁኑ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ አሜን።
፵፭. የአምላካችን የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር አብ ይክበር ይመስገን አሜን።
፵፮. ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው የአብ የባሕርይ አንድ ልጁ የሚሆን እግዚአብሔር ወልድም ይክበር ይመስገን አሜን።
፵፯. የአብና የወልድ የባሕርይ ሕይወታቸው የሚሆን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ይክበር ይመስገን አሜን።
፵፰. አብ የባሕርይ አምላክ ነው የጌትነቱም ዙፋን ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ትክክል ነው።
፵፱. ወልድ የባሕርይ አምላክ ነው የጌትነቱም ዙፋን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ትክክል ነው።
፶. መንፈስ ቅዱስም የባሕርይ አምላክ ነው የጌትነቱ ዙፋንም ከአብ ከወልድ ጋር ትክክል ነው።
፶፩. እንግዲህ በአንድ የጌትነት ዙፋን ላይ የአካል ሦስትነትና የመለኮት አንድነት እንዳለ እናምናለን።
፶፪. ለማይጠቀለል ለሥላሴ አንድነት ምስጋና ይገባል።
፶፫. ለማይከፋፈል ለሥላሴ ሦስትነት ምስጋና ይገባል።
፶፬. የዝርውነት ባሕርይ ለሌለው ለሥላሴ ሐሳብ ምስጋና ይገባል።
፶፭. ለማይመረመር ለሥላሴ አነዋወር ምስጋና ይገባል።
፶፮. ሰማይና ምድር ለማይወስኑት ለአካለ ሥላሴ ምስጋና ይገባል።
፶፯. ተመራምሮ ለማይደረስበት ለሥላሴ ቅድምና ምስጋና ይገባል።
፶፰. ኅልፈት ውላጤ ለሌለበት ለሥላሴ መንግሥት ምስጋና ይገባል።
፶፱. ልዩ ተጨማሪ ስም ለማያስፈልገው (ለማይስማማው) ለሥላሴ ምስጋና ይገባል።
፷. ከፍጹም ሦስትነት ወደ ዐራተኛነት ከፍ ለማይል ፍጹም የስም ሦስትነት ምስጋና ይገባል።
፷፩. ከፍጹም የገጽ ሦስትነት ወደ ሁለተኝነት ገጽ ዝቅ ለማይል የገጽ ሦስትነት ምስጋና ይገባል።
፷፪. ለማይወሰን ለሥላሴ ቸርነት ምስጋና ይገባል።
፷፫. ልዩ ሦስት ለሚሆኑ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል።
፷፬. በልዩ የነደ እሳት ነፀብራቅ ለተከበበችና ሁሉ በሁሉ ሙሉ ለሆነች ሥላሴነት ምስጋና ይገባል። ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን።